ኢየሱስ አማላጅ?

kmichael

kmichael

· 14 min read
Thumbnail

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን። በዚህ ፅሁፍ ጌታ በፈቀደና በረዳን መጠን "ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፈራጅ ነው ወይንስ አማላጅ? " የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ እንሞክራለን። ጌታ መንፈስቅዱስ አይነ ልቦናችንን ከፍቶ እዉነትን አንድንረዳ ይፍቀድልን ።

ይህ " ኢየሱስ ፈራጅ ወይ አማላጅ " ሙግት በተለይ በኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ምዕመናን እና በፕሮቴስታንት አማኞች መካከል ሲዘወተር ይስተዋላል :: ይህ ክርክር መሠረታዊ ምንጩ የሁለቱ እምነቶች መሠረታዊ የነገረ ድህነት አስምህሮ ልዩነት እና በሚደረጉት ክርክሮች " ምልጃ " በሁለቱ ቤተ እምነቶች ዘንድ ያለዉ ትርጓሜ ልዩነት እንዳለው ይስተዋላል :: በሌላ አነጋገር አንድ አካል "አማለደ" ሲባል ምን ማለት ነው ለሚለው ጥያቄ የሚሠጡት መልስ ዥንጉርጉር ነው። የተዋጣለት ውይይት ለማድረግ ደግሞ ቢያንስ በቃላት ትርጉም መስማማት የግድ ይላል።

ይህንንም በመረዳት ጥያቄውን ቀጥታ ከመመለሣችን በፊት ለመልሱ መንገድ የሚጠርጉ ጥያቄዎችን በመጠየቅ እንጀምራለን። ከላይ እንደጠቀስነው የጥያቄው ምንጭ ከ ዶግማ ለዩነትና ከቃላት ትርጓሜ ልዩነት ስለሚመነጭ ቢያንስ የሚከተሉትን ጥያቄዎች በመመለስ መንሳት ይኖርብናል ::

ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው

ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና ጌታችን አምላካችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በስጋ ከተገለጠ አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ ስለ ማንነቱ ብዙዎች ይከራከራሉ። ብዙዎች አብረውት ውለው አድረው አላወቁትም ፣ ብዙዎችም ተሰናክለውበታል፣ የተፈቀደላቸው ና የተገለጠላቸውም ሙሉ ማንነቱን አውቀው ተረድተው ህይወትን ወርሰዋል፡፡ የእርሱን ማንነት ማወቅና መረዳት የድህነታችን ሁሉ መሠረት ነው :: ለዚህም ነው በሚቴዎስ ወንጌል ተፅፎ እንደምናነበው ጌታ ሐዋርያትን ሰዎች እርሱን ማን ብለው እንደሚያስቡት የጠየቃቸው።

ኢየሱስም ወደ ፊልጶስ ቂሣርያ አገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን። ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደ ሆነ ይሉታል? ብሎ ጠየቀ። እነርሱም። አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ አሉት። እርሱም። እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው። ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ። አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ አለ። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው። የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ። እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም።ማቴ 16: 13 - 18

ሃዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ ብሎ በመለሠለት ጊዜ ጌታ መልሶ ይህንን አብ እንጂ ምድራዊ እውቀት እንዳልገለጠለት ሲያስርግጥለት እናያለን :: ይህንንም እዉነት በተረዳው በጴጥሮስ ላይ ቅድስት ቤተክርስቲያንን ሲመሠረታት እንመለከታለን :: ይህ እውነት የእምነታችን መሠረት ነው። ጴጥሮስን አለት ያደረገው እዉነት ኢየሱስ ክርስቶስ የህያው የእግዚአብሔር ልጅ ነው የሚለው ነው ::

ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው ስንል አርዮሳውያን እንደሚሉት ሳይሆን በሃይማኖት መሠረት (ፀሎተ ሃይማኖት ) ላይ እንደተቀመጠልን " ሰማይና ምድርን የፈጠረ፣ የሚታየውንና የማይታየውንም ዓለም ሳይፈጠር ከርሱ ጋር በነበረ፣ አንድ የአብ ልጅ በሚሆን በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን። ከብርሃን የተገኘ ብርሃን፣ ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ አምላክ፣ የተወለደ እንጂ ያልተፈጠረ፣ በባሕርዩ ከአብ ጋር የሚተካከል፣ ሁሉ በእርሱ የሆነ፣ በሰማይም ካለው በምድርም ካለው ያለ እርሱ ምንም የሆነ የለም። ስለኛ ስለ ሰዎች እኛን ለማዳን ከሰማይ ወረደ። በመንፈስ ቅዱስ ግብር ከቅድስት ድንግል ማርያም ፍፁም ሰው ሆነ" ብለን ነው የምናምነው :: ኢየሱስ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ትክክል ነው :: በግብር አብ ወላዲ ወልድ ተወላዲ መንፈስ ቅዱስ ሰራፂ ቢሆኑም በመለኮት በስልጣን በአገዛዝ በፈቃድ አንድ ናቸው::

አባ ህርያቆስ በቅዳሴው እንዲህ እንዳለ " የላከ አብን በህላዌው አባት እንደሆነ እናምናለን ፤ የተላከ ወልድንም በህላዌው ወልድ እንደሆነ እናምናለን ፤ ማሕየዊ መንፈስ ቅዱስንም በህላዌው መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ እናምናለን፡፡ ሶስቱ ስም አንዱ እግዚአብሄር ነው፡፡ አብርሃም ከይስሐቅ እንደሚበልጥ ፡ ይስሐቅም ከያእቆብ እንደሚበልጥ አይደለም፡፡ ለመለኮት እንዲህ አይደለም ፡ አብ ከልጁ አይበልጥም፡፡ ወልድም ከመንፈስ ቅዱስ አይበልጥም ፤ መንፈስ ቅዱስም ከወልድ አያንስም ፤ ወልድም ከአባቱ አያንስም፡፡ መለኮት ግን አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ አንድ አምላክ ፡ አንዲት መንግስት ፡ አንዲት ስልጣን ፡ አንዲት አገዛዝ ናቸው " ::

ይህንን ደጋግመን ያነሳነው የኢየሱስን ፍፁም አምላክነት ያለ ምንም ጥርጥር አስረግጠን ማለፍ ስላለብን ነው :: ኢየሱስ ክርስቶስ በራሱ ማድረግ የማይችለው አንዳች ነገር አለ ብሎ ማሰብ ምንፍቅና መሆኑ ሊታወቅ ስለሚገባ ነው፡፡ ወልድ በተለየ አካሉ ስጋን መዋሃዱ ከአብ የሚያሳንሰው አይደለም :: እንደ " Eternal Subordination " አይነት " አብ በስላሴ አካል ውስጥ የበላይ አስተዳደሪ ነው " የሚሉ ትምህርቶች ከዲያቢሎስ ናቸው :: በስጋው ወራት እኛን ለማዳን ክብሩን ተወ ፣ ከሃጥያት በቀር ፍፁም እኛን ሆነ እንጂ አምላክነቱ ለቅፅበት አልተቋረጠም :: ከዘልአለም እስከ ዘልአለም አምላክ ነው፡ ፡ ለስም አጠራሩ ምስጋና ይግባው። አሜን!

ምልጃ ምንድር ነው

የምልጃ ቅጥተኛ ትርጉም ምንድነው

የምልጃን ቀጥተኛ ትርጉም ስንመለከት አንዱ ስለ ሌላው ለመነ ማለት ነው:: ይህንንም ለማስረዳት በተደጋጋሚ የሚነሳውን የሮሜ 8: 34 ን ጥቅስ እንመልከት

34 የሞተው፥ ይልቁንም ከሙታን የተነሣው፥ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፥ ደግሞ ስለ እኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው።
ሮሜ 8:34

ይህን ማለደ የሚለውን ቃል የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል ያሳተመው የአማርኛ መዝገበ ቃላት ገጽ 70 ላይ እንዲህ ሲል ይፈታዋል

ምልጃ : ልመና ደጅ ጥናት
ማለደ : ለመነ ደጅ ጠና

ይህንን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ የእንግሊዝኛው ትርጓሜ እንዲህ ሲል ያስቀምጠዋል

34 Who is he that condemneth? It is Christ that died, yea rather, that is risen again, who is even at the right hand of God, who also maketh intercession for us.
Romans 8:34

የሚማልደው ለሚለው ቃል አቻ ሆኖ የገባው "maketh intercession" (ሜክስ ኢንተሌሽን) የሚለው ቃል የእንግሊዘኛው Oxford መዝገበ ቃላት እንዴት እንደሚፈታው እንመልከት

​intercession : (with somebody/something) (for/on behalf of somebody/something) the act of speaking to somebody in order to persuade them to be kind to somebody else or to help settle an argument.
  • He was released owing to English intercession with the French.
  • the intercession of a priest

በዚህ መንገድ የቃሉን ትርጓሜ በግልጽ ካሳየን በኋላ "ኢየሱስ አማላጅ ነው ወይስ ፈራጅ ብሎ?" አንድ ሰው ሲጠይቅ ወደ መልስ ከመግባት በፊት አማላጅ ስትል (ስትይ) ምን ለማለት ነው ተብሎ መጠየቅ አለበት። የዚህም መልሱ ከሚከተሉት አንዱ ነው ( በአብዛኛው )።

  • ከአብ ጋር አማልዶናል (አስታርቆናል) ስለዚህ አማላጅ ልንለው እንችላለን (ይገባል)
  • ዛሬም ድረስ ያማልደናል (ያስታርቀናል)
  • ዛሬም ድረስ ያማልዳል (አብን ይለምንልናል)

ኢየሱስ አስታርቆናልን?

አዎ ሰውና እግዚአብሔር የታረቁት በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ መላእክት በፊቱ በመንቀጥቀጥ የሚቆሙለት ፣ የሚያመሰግኑት ፣ የሚሰግዱለት አምላክ ሆኖ ሳለ እኛን ለማዳን ሲል ከሰማይ ሰማያት ወረደ ቦታና ጊዜ የማይወስኑት ጌታ በአንዲት ድንግል ማህፀን ተወሰነ በበረት ተወለደ እንደ ሰው ቀስ በቀስ አደገ በሰውነቱ ከሃጥያት በቀር ሰው የሆነውን ሁሉ ሆነ በላ፣ ጠጣ ፣ እንደኛ ሣቀ አዘነ :: በሠላሣ ዘመኑ በዮርዳኖስ ተጠመቀ በገዳመ ቆሮንቶስ አርባ ቀን አርባ ሌሊት ፆመ በዲያቢሎስ ተፈተነ ድልም ነሣው። በመካከላችን ተመላልሥ የማይታየውን የእግዚአብሄርን መልክ አሣየን :: በእለተ አርብ እራሱ መስዋዕት አቅራቢ ሊቀ ካህን ፣ እራሱ አማናዊ ቅዱስ መስዋዕት እንዲሁም ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እራሱ መስዋዕት ተቀባይ ሆኖ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አድኖናል፡ አስታርቆናል :: በላያችን ላይ ነግሥ ይኖር የነበረን የሞትና የጨለማ ሃይል ድል ነስቶልናል :: ሞት ተሸንፏል :: ብርሃን ወጥተልናን። የልጅነትን ፀጋ ዳግም አገኝተናል ። በዚህም ከእግዚአብሔር ጋር ታርቀናል :: በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የነበረው የጥል ግድግዳ ሰውና እግዚአብሔር በሆነው በኢየሱስ (መካከለኛ ሆኖ) ፈርሷል።

ኢየሱስ ለምኖልናልን ?

እግዚአብሄር ወልድ ሰዉ ሆኗል ስንል ለይስሙላ አይደለም :: ፍፁም እኛን ሆኗል:: ወገናችን ወንድማችን ወዳጃችን ሆኗል። ሃዘናችን አሳዝኖታል ደስታችን አስደስቶታል :: አዎ ጌታችን በስጋው ወራት ስለኛ ወደ አብ ፀሎትን አቅርቧል። አንድም መምህር እንደመሆኑ ምሳሌ ለመሆን ከዛም በተጨማሪ እንደማዳኑ ስራ አንድ አካል በኛ ቦታ ሆኖ እንደተሰቀለ በእኛ ቦታ ሆኖ ስለኛ ለምኗል።

የጌታ ምርጥ እቃ ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራውያን በፃፈው መልዕክቱ ጌታ በስጋው ወራት ምልጃን እና ፀሎትን እንዳቀረበ በግልፅ ያብራራል።

እርሱም በስጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፥ እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ ተሰማለት፤ዕብ 5:7

በሉቃስ ወንጌል ደግሞ ጌታ በራሱ አንደበት ለ ጴጥሮስ ስለ እነርሱ ማማለዱን ሲነግረው እናያለን።

ጌታም። ስምዖን ስምዖን ሆይ፥ እነሆ፥ ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ለመነ፤ እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ አማለድሁ፤ አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አጽና አለ።ሉቃ 22 : 31-32

እንዲህ ያሉ ብዙ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል :: ጌታችን በተደጋጋሚ በዙሪያው ለነበሩና ለጠቅላላ ለሰው ልጆች ምልጃን ፀሎትን አቅርቧል ::

ኢየሱስም። አባት ሆይ፥ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው አለ።የሉቃስ ወንጌል 23:34
ከዚህም በኋላ በዓለም አይደለሁም፥ እነርሱም በዓለም ናቸው፥ እኔም ወደ አንተ እመጣለሁ። ቅዱስ አባት ሆይ፥ እነዚህን የሰጠኸኝን እንደ እኛ አንድ እንዲሆኑ በስምህ ጠብቃቸው።ዮሐ 17:11
ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ፥ ከቃላቸው የተነሣ በእኔ ስለሚያምኑ ደግሞ እንጂ ስለ እነዚህ ብቻ አልለምንም፤ አንተ እንደ ላክኸኝ ዓለም ያምን ዘንድ፥ አንተ፥ አባት ሆይ፥ በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ፥ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ እለምናለሁ።ዮሐ 17:20-21

ጌታ በስጋው ወራት ፀሎትንና ምልጃን ማቅርቡን በዚህ ካየን ይህንን ያደረገበት ምክያት ማስተዋሉ ይጠቅመናል። እግዚብሄር ወልድ በስጋ ሲገለጥ ለአንድ ታላቅ አላማ ይህም አለምን ለማዳን ነው። በስጋ የተገለጠው የአብ ቃል ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ቢሆንም የማዳኑ ስራ ግን የቅድስት ስላሴ የአብ የወልድም የመንፈስ ቅዱስም ነው :: በሦስቱ መካከል መለያየት የለምና። በዚህ በማዳን ስራ ውስጥ አብን ከወልድ ወልድን ከመንፈስ ቅዱስ ከመነጣጠል መጠንቀቅ ይገባል። አንዳንዶች በማወቅም ባለማወቅም አብ ቁጡ ሆኖ ወልድ ግን ሩህሩህ ሆኖ የአብን ቁጣ ሊያበርድ እንደመጣ አድርገው የሚያስተምሩ አሉና እንጠንቀቅ :: በመስቀል ዋጋ የከፈለ ደም ያፈሰሰ ስጋ የቆረሰ ወልድ ኢየሱስ ቢሆነም ፍቃዱ ፣ አላማው ፣ ጠቅላላ የማዳኑ ስራ የአብም የወልድም የመንፈስ ቅዱስም (የእግዚአብሔር ) ነው። አባታችን ቅዱስ አፍሬም በማክሰኞ ውዳሴ ማርያም ድርሰቱ "በእርሱ ፈቃድ በአባቱም ፈቃድ በመንፈስ ቅዱሱም ፈቃድ መጥቶ አዳነን" እንዳለ ። ለዚህ ነው እግዚአብሄር (አብ ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ) በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበር ብሎ ቅዱስ ጳውሎስ በቆሮንቶስ መልዕክቱ የሚነግረን

" እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ።"2ኛ ቆሮ 5:19

ዛሬም ድረስ ያስታርቀናል

በብሉይ ኪዳን አይሁድ ከእግዚአብሄር ጋር በነበራቸው ኪዳን መሠረት ስለ ሃጥያታቸው ስርየት የእንስሳትን ደም ይሰዉ ነበር :: ይህ በአመት አንዴ ስለ ህዝቡ ሁሉ ሃጥያት ይደረግ ነበር :: ይሁንና ይህ የእስሳት ደም ከሰዎች ተላይቶ የነበረን የእግዚአብሔር ፀጋ የሚመልስ አልነበረም :: ከጊዜያዊ የእግዚአብሄር ቍጣ የሚያድን እንጂ ።

" ስለ ሕዝቡም ኃጢአት የሚሠዋውን መሥዋዕት ፍየል ያርዳል፥ ደሙም ወደ መጋረጃው ውስጥ ያመጣዋል፤ በወይፈኑም ደም እንዳደረገ በፍየሉ ደም ያደርጋል፤ በመክደኛውም ላይና በመክደኛውም ፊት ይረጨዋል።"ዘሌ 16:15
" የሥጋ ሕይወት በደሙ ውስጥ ነውና፤ ደሙም ከሕይወቱ የተነሣ ያስተሰርያልና በመሠዊያው ላይ ለነፍሳችሁ ማስተስረያ ይሆን ዘንድ እኔ ለእናንተ ሰጠሁት።"ዘሌ 17:11

ይህ በአመት አንዴ ስለ ህዝቡ ሁሉ ሃጥያት ይደረግ ነበር :: ይሁንና ይህ የእስሳት ደም ከሰዎች ተለይቶ የነበረን የእግዚአብሔር ፀጋ የሚመልስ አልነበረም :: ከጊዜያዊ የእግዚአብሄር ቍጣን የሚያስቀር እንጂ ።

ይህንንም አይተው ነብያት አማናዊውን እና ለዘልአለም በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ሰላምን የሚያወርደውን መሲሕ ሲጠባበቁ ኖረዋል። ከነዚህም የእግዚአብሔርን መሲህ ሳያይ እንደማይሞት መንፈስ ቅዱስ የነገረው አረጋዊው ስምኦን ቀድሞ በነብያት ትንቢት የተነገረለት የሰው ልጅ የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ ስለመወለዱ ምስክር ሆነ፡፡

እነሆም፥ በኢየሩሳሌም ስምዖን የሚባል ሰው ነበረ፥ ይህም ሰው የእስራኤልን መጽናናት ይጠባበቅ ነበር፤ ጻድቅና ትጉህም ነበረ፥ መንፈስ ቅዱስም በእርሱ ላይ ነበረ። በጌታም የተቀባውን ሳያይ ሞትን እንዳያይ በመንፈስ ቅዱስ ተረድቶ ነበር። በመንፈስም ወደ መቅደስ ወጣ፤ ወላጆቹም እንደ ሕጉ ልማድ ያደርጉለት ዘንድ ሕፃኑን ኢየሱስን በአስገቡት ጊዜ፥ እርሱ ደግሞ ተቀብሎ አቀፈው እግዚአብሔርንም እየባረከ እንዲህ አለ። ጌታ ሆይ፥ አሁን እንደ ቃልህ ባሪያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ፤ ዓይኖቼ በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን ማዳንህን አይተዋልና፤ ይህም ለአሕዛብ ሁሉን የሚገልጥ ብርሃን ለሕዝብህም ለእስራኤል ክብር ነው።
ሉቃ 2፥ 25- 32

እነሆ የመዳናችን ታሪክ መልካም ዜና በጌታ መወለድ ተጀመረ :: ጌታም በክብርና በሞገስ በጥቂት በጥቂቱ አድጎ አገልግሎቱን በሰው ሁሉ ፊት በይፋ በ30 ዘመኑ ጀመረ። ለዚህም አገልግሎቱ መንገድ ጠራጊ የተባለ መጥምቁ ቅዱስ ዮሃንስ ሲጠበቅ የነበረው የሰውን ሃጢያት የሚያስወግድ መሲሕ መገለጡን አበሰረን ::

በነገው ዮሐንስ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ። እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ።
ዮሐ 1:29

ይህም ትንቢት በዕለተ አርብ በቀራኒዮ ጌታ በመስቀል ላይ ህይወቱን ለሰው ልጆች ሁሉ መስዋዕት አድርጎ ሲያቀርብ ተፈጸመ። ይህ መስዋዕት ግን እንደ ወይፈንና ፍየል ደም ለአንድ አመት ብቻ የሚያገለግል ፥ በየዓመቱ መደጋገም የሚያስፈልገው ፥ ሊቀ ካህንም አንዱ ሲሞት ሌላ የሚተካለት አይደለም አንድ ጊዜ ለዘልአለም በማይሞት ሊቀካህን የቀረበ ዘልአለማዊ ና አማናዊ የአዲስ ኪዳን መስዋዕት አንጂ።

ቅዱስ ጳውሎስ በእብራውያን መልዕክቱ ይህንን እንዲህ ሲል ያስረዳል።

እንዲሁ ኢየሱስ ለሚሻል ኪዳን ዋስ ሆኖአል። እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው፤ እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል። ቅዱስና ያለ ተንኮል ነውርም የሌለበት ከኃጢአተኞችም የተለየ ከሰማያትም ከፍ ከፍ ያለ፥ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ይገባልና፤ እርሱም እንደነዚያ ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለ ራሱ ኃጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና።
ዕብ 7 ፥ 22 - 27
ሊቀ ካህናትም በየዓመቱ የሌላውን ደም ይዞ ወደ ቅድስት እንደሚገባ፥ ራሱን ብዙ ጊዜ ሊያቀርብ አልገባም፤ እንዲህ ቢሆንስ፥ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ብዙ ጊዜ መከራ ሊቀበል ባስፈለገው ነበር፤ አሁን ግን በዓለም ፍጻሜ ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጦአል። ለሰዎችም አንድ ጊዜ መሞት ከእርሱ በኋላም ፍርድ እንደ ተመደበባቸው፥ እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ፥ የብዙዎችን ኃጢአት ሊሸከም አንድ ጊዜ ከተሰዋ በኋላ፥ ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታይላቸዋል።
ዕብ 9 ፥ 25 - 28

ከላይ በጥቅሱ እንደሚነበበው ጌታችን ኢየሱስ በቀራኒዮ መስቀል ላይ አንድ ጊዜ ለዘላለም የሰው ልጆችን የሚቤዥ መስዋዕትን ማቅረቡን እና እንደ ድሮው ኪዳን በድግግሞሽ ስለ ሃጥያት ስርየት መቅረብ የማያስፈልገው አዲስ ኪዳን መኖሩን ነው። እርሱ ለዘልአለም የሚኖር ሊቀ ካህን ነውና እንደ ድሮው ኪዳን በሞት ምክንያት መተካካት የሚያስፈልገው አይደለም :: አንድ ጊዜ የማማለድን ስራ በመፈጸም ለዘልአለም በዕርሱ ወደ እግዚአብሄር የሚመጡትን ሊያድናቸው ይችላል።

ስለዚህም ጌታችን በምድር ላይ የፈጸመው የማማለድ የማስታረቅ አገልግሎት ለዘልአለም በእርሱ የሚያምኑትን ሁሉ እያዳናቸው (እያስታርቃቸው) ይኖራል። እኔና እናንተም የእግዚአብሔርን ልጅነት ያገኘነው ይህንኑ የማማለድ / የማስታረቅ አገልግሎት ተካፋይ በመሆን ነው ። ልጅነትንም ካገኘን በኋላ ከምንሠራው ኃጥያት በንስሃ ተመልሰን የሃጥያትን ስርየት የምናገኝበት ቅዱስ ሰጋውና ክቡር ደሙ ከዚህ የማስታረቅ አገልግሎት ያገኘነው ነው።

ዛሬም ድረስ አብን ይለምንልናል ?

ይህንን አፍ አውጥተን መመለስ ባይኖርብንም ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ "ያማልዳል " ስንል "ይለምናል " እያልን ከሆነ ተሳስተናል :: ከላይ በተደጋጋሚ የኢየሱስ ክርስቶስን ማንነት አይተናል። በዕይታችንም እርሱ ሁሉን ቻይ አልፋና ኦሜጋ ከአብና መንፈስ ቅዱስ ጋር እኩል ያለ መበላለጥ ያለመቀዳደም ያለመለያየት የሚኖር የዘለአለም አምላክ ነው:: ይህንን ከተረዳን በኋላ "ኢየሱስ አብን ስለ እኛ ዛሬ በአርያም ይለምናልን? " ብለን እራሳችንን እንጠይቅ። ስለምንስ ነው የሚለምነው? አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ ሃሳብ አንድ መንግስት አንድ አገዛዝ ሆነው ሳለ፣ የአብ ሃሣቡ የወልድ የወልድ ሃሳቡ የመንፈስ ቅዱስ ሆኖ ሣለ አባት ሆይ ማርልኝ ይቅር በልልኝ ብሎ የሚለምንበት ምክንያት ምን ይሆን?

በምድር በተመላለሰበት ወራትስ ፍፁም ሰው ሆኗልና ፣ ሊያድነን እራሱን ዝቅ አድርጎ ወክሎናልና ፣ ለማዳኑ አገልግሎት ልመናንና ምልጃን ማቅረብ አንዱ አካል ነበርና ለምኖልናል ፀልዮልናል :: ዛሬ ግን ሁሉን ከፈጸመ ከእግዚአብሄር ጋር ከታረቅን ልጅነትን ካገኘን፣ ሞትና ሃጥያት ድል ከተነሣ በኋላ መለመን እንዳማያስፈልገው ግልፅ ነው ። የዚህም በተጨማሪ ጌታ ከሞት ከተሃሳ በኋላ እንደ በፊቱ የሚደክም የሚራብ የሚጠማ ደካማ ስጋን ይዞ አይደለም :: በአዲስ በከበረ ስጋ እንጂ።

ይህንንም ቅዱስ ጳውሎስ ከላይ እንዳየነው በዕብራውያን መልዕክቱ አንዴ ለዘላለም በአዲስ (እንደ ድሮው መደጋገም በማያስፈልገው ) ኪዳን እንዳስታርቀን እንደማለደን ነግሮናል :: ነገር ግን አሁን በዚህ መልኩ እንደማናውቀው በቆሮንተስ መልዕክቱ እንዲህ ሲል ይነግረናል::

በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ። ስለዚህ እኛ ከአሁን ጀምሮ ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አናውቅም፤ ክርስቶስንም በሥጋ እንደ ሆነ ያወቅነው ብንሆን እንኳ፥ አሁን ግን ከእንግዲህ ወዲህ እንደዚህ አናውቀውም
2ኛ ቆሮ 5 ፥ 15 - 16

ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ሲል ጌታን ከትንሣኤው በፊት እንደተራበ እንደተጠማ እንደፀለየ እንደተማፀነ ራሱን ዝቅ እንዳደረገ ከንግዲህ ወዲህ እንዲህ አነውቀውም ማለቱ ግልፅ ነው ።

ጌታ እራሱም እኛ በስሙ የምንለምነውን እንደሚያደርገው እንጂ አብን እንደማይለምን በግልፅ ነግሮናል ::

በዚያን ቀን በስሜ ትለምናላችሁ፤ እኔም ስለ እናንተ አብን እንድለምን የምላችሁ አይደለሁም፤
ዮሐ ፥ 16:26

እንግዲህ ጌታ እራሱ አልለምንም እያለ አይ ይለምናል ብሎ ማመን (መሟገት) ትክክል አይደለም። ይልቅስ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ እኔው እራሴ አደርገዋለሁ ብሎ ነግሮናልና ኣሜን ብለን ልንቀበለው ይገባል ::

እኔ ወደ አብ እሄዳለሁና፤ አብም ስለ ወልድ እንዲከበር በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ። ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ
ዮሐ 14 ፥ 13 - 14

ታድያ ለምን በሮሜ 8፥34 " ስለ እኛ የሚማልደው " ይላል ከተባለ አዎ ይማልዳል :: አንድ ጊዜ በምድር በሰራው ስራ በተቀበለው መከራ በፈሰሰው ደም በቆረሰው ስጋ ለዘልአለም እየማለደ ይኖራል :: እግዚአብሄር ወልድ ብቻ ሣይሆን መንፈስ ቅዱስ እራሱ በማይነገር መቃተት ስለ እኛ ይማልዳል።

እንዲሁም ደግሞ መንፈስ ድካማችንን ያግዛል፤ እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና፥ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል
ሮሜ 8 ፥ 26

ይህ ማለት ጌታ መንፈስ ቅዱስ በመንፈሳዊ ህይወታችን ያግዘናል ይመራናል ያስተምራናል እንጂ አብን ይለምንልናል ማለት እንዳልሆነ ግልፅ ነው።

ማጠቃላያ

  1. ኢየሱስ ክርስቶስ አስታቆናል ?
    • አዎ በሚገባ: ( ዕብ 5 - 7 , ሉቃ 22:31-32)
  2. ኢየሱስ ክርስቶስ በስጋው በሰራው የማስታረቅ ስራ ዛሬም ድረስ ያስታርቀናል ?
    • አዎ በሚገባ: 7: 22 -27 ,ዕብ 9 : 25 - 28
  3. ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬም በአብ ፊት ቆሞ ይለምናል /ይፀልያል
    • በፍጹም አይደለም: ዮሐ 14 ፥ 13 - 14 , ዮሐ ፥ 16:26

እግዚአብሄር እኛን ከመውደዱ የተነሣ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም ተወልዶ መከራን ተቀብሎ አድኖናል :: ዛሬም እያዳነን ነው ነገም ያድነናል :: በዚህ የማዳን ስራ በሦስቱ የስላሴ አካላት መለያየት የለም። በአንድ አላማ በአንድ ፍቅር እግዚአብሄር በልጁ በኩል አለሙን ከራሱ ጋር አስታቋል ዛሬም በመንፈሱ እያገዘን መንግስቱን ያወርስናል ። እኛም የተሰጠንን ነፃ ስጦታ እንድንጠቀም በንስሃ ህይወት እንድንመላለስ ስጋውን እንድንበላ ደሙንም እንድንጠጣ ከእርሱ ጋር በቅድስና እንድንኖር ጌታ ይርዳን::

ውስብሃት ለእግዚአብሄር ወወላዲቱ ድንግል መመስቀሉ ክቡር :: ይቆየን።

kmichael

About kmichael

Hi I am Kmichael, you can find my content here. happy reading!

Copyright © 2024 Tewahedo Answers. All rights reserved.